ዶክተር አቢይ ዘግይተው የመጡ መሪ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ቁጭ ብዬ ሳስበው:~ አጼ ቴዎድሮስ ከጊዜያቸው ቀድመው የተፈጠሩ መሪ እንደሚባለው ሁሉ ዶ/ር አብይ አህመድ ደግሞ ዘግይተው የተፈጠሩ መሪ ይመስሉኛል።

እኚህ ሰው ከሁለት አስርት አመት በፊት የኢትዮጵያ መሪ ሆነው ቢሆን ኖሮ የሀገራችን ነገር ይህን ያህል ባልከፋ ፖለቲካችንም እንደ እሬት ባልመረረ።

ሰውዬው ላለፉት ሰላሳ ቀናት በየስፍራው እየዞሩ በተለይም በሌሎች ሀገራት ሄደው የሚያነሷቸው ነገሮች ስሜትን ይኮረኩራሉ።

ሱዳን ሄደው ለአመታት በወህኒ የተዘነጉትን ኢትዮጵያውያንን ፍቱልኝ አሉ። ኬኒያ ወርደው “በምንም ምክኒያት ይሁን ሀገራቸውን ጥለው የመጡ ኢትዮጵያውያን በክብር ይያዙ የታሰሩም ይፈቱ” ሲሉ ለኬኒያው መሪ ተናገሩ።

አንድ መሪ ከሰው በላይ ከዜጎቹ በላይ በየቦታው የሚያስበው ምን አለ? መንጌን ዛሬም ድረስ ለምን ወደድነው? ” ህዝቤ እኔን ጠልቶ እንጂ ሀገሩን ጠልቶ አይደለም እዚህ ያለው። ከዚህ በሁዋላ ፖሊሶቻችሁ በኢትዮጵያውያን ላይ አንዳች ነገር ቢያደርጉ አንድ ሚግ ብቻ ይበቃኛል” ብሎ ለቀድሞው የኬኒያው መሪ ማስጠንቀቅያ ልኮ የዜጎቹን ክብር በሰው መሬት ላይ በማስጠበቁ አይደለም?

….እና አብይ አህመድ ያረፈዱ መሪ፣ ኢትዮጵያን እና ዜጎቿን ያስቀደሙ ናቸው።….ከውጥንቅጡ የፖለቲካ ውጥረት ዞር ብለን ስናያቸው ሰውዬው ከዝያ ዘመን ጋር የተማሰሉ፣ ዜጋና ዜግነት ሀገርና ኩራት በገነነበት ሰአት መፈጠር የሚገባቸው፣ መሪ አልባ ስንሆን መሪ ለመሆን ከድሮው ተቀንሰው የቀሩልን ሁነኛ ሰው ናቸው።

(የትነበርክ ታደለ)

Share.

About Author

Leave A Reply