ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ: የኦርቶዶክሳውያን ይኹንታና ውክልና የተሰጣቸው ምእመናን፣ ሊቃውንትና ምሁራን የሚሳተፉበት ሕዝባዊ ሲኖዶስ እንዲቋቋም ጠየቁ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የጽሁፉ ዋና ዋና ነጥቦች በሐራ ተዋሕዶ የቀረበውን ይመልከቱና ከታች ሙሉ ጽሁፉን ያንብቡት::

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሳይኾን የግለሰቦች ፍላጎትና ጥቅም የሚዘውረው ከኾነ እግዚአብሔር ስለማይደሰትበት፣ ልዕልናው እና ቅድስናው አጠያያቂ ይኾናል፤
ይህን አሠራር እግዚአብሔር ስለማይደሰትበት፣ ቡራኬውን ወደ እርግማን ይቀይረዋል፤እናስተምር ቢሉ አእምሮውን ጥበቡን ይነሳቸዋል፤ ጩኸታቸውንም የማይሰማቸው ይኾናሉ፤
ምእመኑን በትውልዱና በጎሣው ምክንያት እየለዩ ጭፍን ጥላቻ የሚያንጸባርቁና ከሕግ አግባብ ውጭ የኾኑ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ማየት ብርቃችን አይደለም፤
ገንዘብና ዘመድ የሌላቸው ሊቃውንትና ካህናት፣ ፍትሕን ፍለጋ የሚንገላቱት የተለየ በደል ፈጽመው ሳይኾን፣ ከጎሣና ጥቅም የጸዳ አባትና ሲኖዶሳዊ አካል ስላጡ ብቻ ነው፤
“እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል”የሚለውን የሐዋርያትን የጉባኤ ቃል ለይምሰል እየጠቀሱ በዋጋ የሚያስተምሩ አባቶችን መመልከታችን የትንቢቱ ፍጻሜ ላይ መድረሳችንን ያረጋግጣል፤
“የአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ለሠራተኛ ቅጥር 100ሺሕ ብር ጉቦ መቀበሉ ታወቀ” ሲባል፣ ያሰናብቱታል ወይም አግደው ጉዳዩን ያጣሩታል ብለን ገምተን ነበር፤ ለካ ሰውዬው ጎይትኦም እንጂ ዘሪሁን ባለመኾኑ ግምታችን ሳይሳካ ቀርቷል፤
ይህ፣ ከማንነትህ ጋራ ተያይዞ የሚመጣብህ ዕዳ ነው፤ እንደ ሥራ አስኪያጁ ዓይነት ስምና ማንነት ሲኖርህ፣ በአባ ሆይ ችሎት ዘንድ ያለመከሠስ ጸጋ እንዳለህ ያመላክታል፤
የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ፣ በዓለማዊ ፍርድ ቤትና ገዢዎች ዘንድ እንዲያዝ ማድረግ፣ ከጳጳሳቱ ጉባኤ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ይጠበቃልን?

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለግፉዓን ፍትሕ አለመስጠቱ፣ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየመጣ ያለውን ተቋማዊ ክስረት ማሳያ እንደኾነ ልንረዳው ይገባል!!
“ክርስቶስ አማላጅ ነው” የሚል መጽሐፍ የጻፈና የሚያስተ
ምር መምህር በመንፈሳዊ ኮሌጅ መቀጠሩን እያወቃችሁ ዝም ያላችሁት ግለሰባዊ አካሔድ ላይ ስለምታተኩሩ ነው፤
ስለተሾሙለት ሕዝብ ሳይኾን ባሕር ማዶ ለመሻገር የምረጡኝ ዘመቻ በአሁኑ የጳጳሳቱ ጉባኤ የተሰማ አይደለምን? ሓላፊነት እየደራረቡ ሁለት ሦስት ደመወዝ መውሰድስ የጽድቅ ነው?
የምእመናን አቤቱታ እንዳይሰማ፣ “የአባ እገሌ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው፤” እየተባለ አህጉረ ስብከት ከሲኖዶሳዊ አሠራር ውጭ ኾነው በጳጳሳቱ ይኹንታ ብቻ የሚተዳደሩበትስ ቀኖና አለን?
ከዓመት እስከ ዓመት የሚንከባለሉ ችግሮችን ማየታችን፣ ሲኖዶሱ ፍትሕን ለመስጠት ያለውን ልዕልና በግለሰቦች ፍላጎት ሥር እንዳዋለው ሊያስረዳን ይችላል፡፡
ይህ ከሚያስከትለው አደጋ አንዱ፣ የቤተ ክርስቲያን በዓለማዊ ፍ/ቤት መዳኘትና ምእመናን እየተፈራረሙና እያስወሰኑ በቦርድ እንድትመራ ማድረግ መኾኑ ሩቅ አይመስልም፡፡
በቤተ ክርስቲያን ችግሮች ውሳኔ የማትሰጡ ከኾነ እናንተ እነማን ናችሁ? የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የማያሳስባችሁ ከኾነና ከምእመናን ጋራ የምትገናኙበት መንገድ እየተቋረጠ ከሔደ…
…ማኅበረ ምእመናኑ ያመኑበት፣ ለአመራሩና ውሳኔው የሚገዙለት፣ ይኹንታና ውክልና የሰጣቸው ሊቃውንትና ምሁራን የሚሳተፉበት ሕዝባዊ ሲኖዶስ ሊቋቋም ይገባል፡፡
“ሕዝባዊ ሲኖዶስ ሊቋቋም ይገባል”
ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ

(የጥንታውያን ቋንቋዎችና ጽሑፎች ተመራማሪ)

(ግዮን መጽሔት፤ ቅጽ ፩ ቄጥር ፮፤ ግንቦት ፳፻፲ ዓ.ም.)

ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት የተቀደሰ ጉባኤ ማለት ነው፡፡ በፍትሐ ነገሥቱ እንደተደነገገው፣ ሲኖዶስ ማለት ቃሉ የግሪክ ሲኾን፣ ትርጉሙም የጳጳሳትና የሊቃውንት ማኅበር ወይም ሸንጎ ወይም ስብሰባ አልያም ጉባኤ ማለት ነው:: በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሔደው የጳጳሳት ጉባኤ መጠርያም ነው፡፡

ይህ ጉባኤ ታሪካዊ አመጣጡ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ያለ ሲኾን፣ ከጥንት ጀምሮ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ እንከን የለሽ ውሳኔ የሚተላለፍበት፤ ሁሉን በእኩልነት የሚያይ ጉባኤ ነው፡፡ ኾኖም በቅዱስ ሲኖዶስ ስም እንደ ዓለማውያኑ ሸንጎ፣ የሐሰትና የቡድን ውሳኔ የሚተላለፍበት፣ መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሳይኾን የግለሰቦች ፍላጎትና ጥቅም የሚዘውረው ከኾነ እግዚአብሔር ስለማይደሰትበት ልዕልናውና ቅድስናው አጠያያቂ ይኾናል፡፡

በትንቢተ አሞጽ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው፣ እስራኤላውያን እንደዚህ ዓይነት ቅዱስ ጉባኤ በመረጡት ቀን ያደርጉና “እግዚአብሔር ተናገረ፤ ፍርድንም ሰጠ” ብለው ያውጁ ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በመንፈሳዊ አቋማቸውና በቅዱስ ሲኖዶሳቸው ስም የሚያካሒዱት ሃይማኖታዊ ያሉትን ተግባራትና ውሳኔአቸውን  ተቃውሟቸዋል፡፡ ይልቁንም፣ በእግዚአብሔር ቀን የእግዚአብሔር ፍርድ እያሉ የሚመኩበትን ቅዱስ ጉባኤን በተመለከተ፣ “የተቀደሰው ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም” በማለት ቃል በቃል ገሥጾአቸዋል፤ የጉባኤያቸውንም ውሳኔ  እስከነድርጊቱ ነቅፎታል፤ ይልቁንም ፍትሕን እስካለመጡና የተበደለን እስካልካሱ ድረስ መሥዋዕታቸውን፣ ዝማሬአቸውንና ቊርባናቸውን እንደማይቀበለው አስታውቋቸዋል፡፡

ይህ ዓይነቱን ሲኖዶሳዊ አሠራር እግዚአብሔር አይደሰትበትም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ቅዱስ በተባለው ጉባኤ፣ ጉቡዓን የሃይማኖት መሪዎች ቢባርኩ፣ እግዚአብሔር ቡራኬያቸውን ወደ እርግማን  ይቀይረዋል፤ ቅዳሴያቸውን እግዚአብሔር አይቀበለውም፤ ወንጌል እናስተምር ቢሉ አእምሮውን ጥበቡን ይነሳቸዋል፤  እንዘምር፣ ማሕሌት እንቁም ቢሉ፣ ይጮኻሉ ይጮኻሉ፤ እንዳልጮኹ ኾነው እግዚአብሔር የማይሰማቸው ይኾናሉ፡፡

ዛሬ በብሔር ማንነቱ፣ በትውልድ ስፍራው፣ በጎሣ መሠረቱ ምክንያት ምእመኑን እየለዩ ጭፍን ጥላቻ የሚያንጸባርቁና በማን አለብኝነት ከሕግ አግባብ ውጭ የኾኑ የሃይማኖት መሪዎችና የሲኖዶስ አባላት  የኾኑትን እነአቡኑን የዚህ ጉባኤ አባል ኾነው ማየት ብርቃችን አይደለም፡፡ በየፍርድ ቤቱ ፍትሕ ፈልገው የሚንገላቱት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና ገንዘብና ዘመድ የሌላቸው ካህናት ከሌላው የተለየ በደል ሠርተው አይደለም፤ በየሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች የሚመላለሱበት ምክንያታቸው የፓትርያርኩን አባትነት ጠልተውም አልነበረም፤ እንደ ሃይማኖታቸውም የጳጳሳቱን አባትነትና ቡራኬ ሳይፈልጉት ቀርተው አይደለም፤ ነገር ግን ከጎሣና ከጥቅማጥቅም በጸዳ መልኩ ፍትሕ የሚሰጣቸው አባት ወይም የበላይ ሲኖዶሳዊ አካል ስላጡ ብቻ ነው፡፡

ይኸውም ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ኾነ፡፡ በእግዚአብሔር ጉባኤ ውስጥ ተሰብስበው በዋጋ በሚሠሩ፣ የሃይማኖት መሪዎቻችን ምክንያት፣ የምእመናን መጠጊያ የኾነችው ቤተ ክርስቲያን በኑፋቄ፣ በሙስና እና በጎሠኝነት ልትታመስና በኢየሩሳሌም አምሳል የምትታወቀው የእግዚአብሔር ሀገር ኢትዮጵያም የድንጋይ ክምር ልትኾን እንደምትችል በትንቢተ ሚክያስ ተጽፏል፡፡ ይህም የትንቢት ፍጻሜ እየኾነ ያለው፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው፤ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል” የሚለውን የሐዋርያትን የጉባኤ ቃል ለይምሰል እየጠቀሱ ነገር ግን ማንነታቸውን ለዋጋ የሰጡ፣ በጉቦ የሚፈርዱ በዋጋ የሚያስተምሩ የሃይማኖት አባቶችን መመልከታችን የትንቢቱ ፍጻሜ ላይ መድረሳችንን ያረጋግጣል፡፡

ምንጊዜም ጸላኤ ሠናይ ውክልናውን የሚያሳየው ገንዘብ በሚወዱ ሰዎች ነው፡፡ ገንዘብን መውደድ ደግሞ የጥፋት ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ዛሬ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር የጥፋት መሠረት ኾኖ የሚያተራምሰው፣ አፍቅሮተ ንዋይ(የገንዘብ መውደድ) ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተሠየሙ ሰዎች የአስተዳደር ማጠንጠኛቸው የገንዘቡ መጠን እስከኾነ ድረስ  ደግሞ  ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ፣ ማኅበረ ምእመናንን ለመበታተን አባቶች በጨረታው የሚገደዱ ኾነው አላገኘናቸውም፡፡

እንደ ፍትሐ ነገሥት ገለጻ፣ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል የሚያመለክተው የምእመናንን ኅብረት እስከ ኾነ ድረስ፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና አስተዳደሩ መንፈሳዊነቱንና አንድነቱን እንዳያጣ ጳጳሱ በተሾመባቸው ምእመናን ላይ  ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ድንጋጌው ያስጠነቅቃል፡፡ የፍትሕ መንፈሳዊ ሥርዐት ይህ በኾነበት ኹኔታ አንዳንድ ጳጳሳት ግን፣ የቤተ ክርስቲያን አባልና አካል ከኾኑ ማኅበረ ምእመናን ይልቅ በጣት የሚቆጠሩ ነገረ ሠሪዎችን የመረጡበት ምክንያት በፍትሐ ነገሥቱ ለተዘረዘሩት ለገንዘብ መውደድ ሐሜት እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

ሰሞኑን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ የዜና ዘገባ እንዳነበብነው፣ “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ለሠራተኛ ቅጥር 100ሺሕ ብር ጉቦ መቀበሉ ታወቀ” ሲባል፣ አባ ሆይ፣ ሰውዬውን በአንድ ደብዳቤ ያሰናብቱታል ወይም አግደው ጉዳዩን ያጣሩታል ብለን ገምተን ነበር፡፡ ለካ ሰውዬው ጎይትኦም እንጂ  ዘሪሁን ባለመኾኑ ግምታችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ሥራ አስኪያጁ የተዘገበበትን ጥፋት የፈጸመው ግለሰብ፣ የእነእገሌ ወይም የእነእንትና ብሔር ብትኾን ኖሮ፣ እንኳን ታውቆብህ ዜና ኾኖ በተዘገበ ጉዳይ ቀርቶ በፎርጅድ ጉዳይ ከሥራህም ከደመወዝህም ትሰናበታለህ፡፡ ይህ ከማንነትህ ጋራ ተያይዞ የሚመጣብህ ዕዳ ነው፤ እንደ ሥራ አስኪያጁ ዓይነት ስምና ማንነት ሲኖርህ ግን፣ በአባ ሆይ ችሎት ዘንድ ያለመከሠስ ጸጋ እንዳለህ ያመላክታል፡፡ እርሳቸውም ስላንተ ይከራከራሉ፣ መብትህንም ያስከብራሉ፡፡

ሐሜት እንዳይመስልብኝ በእኔ የደረሰውን እንደማሳያ ላቅርብ፡፡አባ ሆይ፣ ባላወቁት ጉዳይ፣ በ2008 ዓ.ም. ከሥራዬ እንድሰናበት ሸኚ ደብዳቤ ጽፈው ስለነበር በነበረኝ የሥራ ክርክር ባላጋራዎቼም የፓትርያርኩ ደብዳቤ አልታየልንም ብለው ይግባኝ ስለጠየቁ አባታችን ስማቸው በፍርድ ቤት በከንቱ እንዳይነሳ በማሰቤ በብዙ ደጅ ጥናት አናግሬአቸው አውቃለሁ፡፡ እርሳቸው ግን ስለ ስማቸውም ስለ መንበረ ክብራቸውም አልተጨነቁም፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ “በምታሸንፍበት መንገድ ሔደህ ልታሸንፍ ትችላለህ” ብለው አሰናበቱኝ፡፡

ፍትሐ ነገሥቱ እንደሚለው፣ “ፓትርያርኩ በራሱ ፍርድ ቤት ያስወስን” የሚለው አንቀጽ የቤት ልጆችን የሚመለከት እንጂ እንደ እኔ አይነቱን በእርሳቸው ዘንድ መጻተኛ የኾንኩትን የማይመለከት መኾኑ የገባኝ ያኔ በተለይ አሁን  ነው፡፡ አሁንም፣ እንደ እንጀራ ልጆች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ፍትሕ የሚሰጣቸው አባት፤ የበላይ አካል የኾነ ይግባኝ ሰሚ ሲያጡ ጉዳያቸው በዓለማዊ ፍርድ ቤት እየተያዘ እስከ ሰበር ፍርድ ቤቶች ድረስ መዝለቃቸውና መብታቸውን ማስከበራቸው አይቀሬ ነው፡፡

በዓለማዊ ፍርድ ቤትና ገዢዎች ዘንድ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ እንዲያዝ ማድረግ ማለት ከጳጳሳቱ ጉባኤ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ይጠበቃልን? ወይስ ብፁዕ ቅዱስ ከሚባል መንበር ወይም መንፈሳዊ ልዕልና ላይ አለ ከሚባል የሃይማኖት መሪም እንዲህ ማድረግ ይገባዋልን? የቤተ ክርስቲያን መገለጫ የኾኑት ማኅበረ ምእመናን፣ መብታቸውን የሚጠይቁት በመንፈሳዊው ልዕልና መንገድ እንዲመለስላቸው በአክብሮት እንጂ በዓለማዊ ፍርድ ቤቶች ፍትሕ እንደሚያገኙ፣ እነርሱም ቢኾን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መኾኑን መንገዱ ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ግን ብፁዕ ቅዱስየሚለው አገላለጽ ለሲኖዶሳዊ መንፈሳዊነት፣ ልዕልናና ለተቋማዊነቱ የተሰጠ በመኾኑንም ቤተ ክርስቲያን ስለ ሁሉም ነገር የፍትሕ ሥርዐት አላት ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡

የሲኖዶሳዊ ሉዓላዊ አሠራር እየቀረ የአብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ ወደ ዓለማዊ አገዛዝ ፍርድ ቤቶች መምራት ማለት፣ የሃይማኖት መሪውን ተቋማዊነት አውርዶ ወደ ግለሰባዊነት ማምጣት ማለት መኾኑን የገባን ስንቶቻችን ነን? በዚህ መንገድ የሃይማኖት መሪዎችም በዓለማዊ አገዛዝ ፍርድ ቤት ከሥሠን ማስቀጣት እንደምንችል የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? መልካም!!! ይህም ቅዱስ ሲኖዶስ ለግፉዓን ፍትሕ አለመስጠቱ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየመጣ ያለውን ተቋማዊ ክስረት ማሳያ መኾኑን ልንረዳው ይገባል!! እናም ታላቁ መጽሐፍ፣ “በመላእክት ላይ እንኳን የመፍረድ ሥልጣን አላችሁ፤” ያለው ከቶ ለማን ነው? ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለፓትርያርኩ አይደለምን? በዚህ ዓለም ጉዳይ በሥርዐታችሁ በአግባቡ መፍረድ ካልቻላችሁ ከዓለማውያን መሪዎች በምን ልትለዩ ትችላላችሁ? ለምእመናን ጥያቄ መፍትሔ እንድታበጁ፣ መናፍቃንን ለይታችሁ እንድታወግዙ፣ ሽማግሌ ሊኾን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ ሊኖር ይገባል፡፡

እንደ መንፈሳዊ መሪነታችሁ፣ በሃይማኖት ጉዳይ የሚተራመሰውን መንፈሳዊ ኮሌጅ ማጥራት ሲገባችሁ  ዝምታን መምረጣችሁ ለምን ይኾን? አሁንም ለአብነት ያህል በመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ከገቡ መምህራን መካከል የአንዱን ቀሣጢ መምህር መጽሐፍ ልጥቀስ፡፡ ይህ ሰው በ2010 ዓ.ም. “መልሕቅ ክፍል ሁለት (አሌትያ)” በሚል መጽሐፉ በገጽ 188 ላይ “ክርስቶስን አማላጅ ነው” ለማለት ሮሜ 8፥34 ላይ ያለውን የሰማንያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይፈርዳልየሚለውን ንባብ ሲተች፣“… ከአተረጓጓም ስልት የራቀ ነው በማለትና ይማልዳል የሚለውን ቁልፍ ሥነ መለኮታዊ  ቃል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን  ይፈርዳል ብለው መቀየር የለባቸውም፤ ተገቢም አይደለም…” በማለት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ2000 ዓመታት በኋላ ቃሉን ኾን ብላ የቀየረች አድርጎ መጻፉና እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ነው ማለቱ የሚያስወግዘው አይደለምን?እንደዚህ ዓይነት የሐሰት ትምህርት የሚያስተምርን በቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መቀጠሩን እያወቃችሁ ዝም ማለታችሁ ለምን ይመስላችኋል?

መጽሐፉን አላነበብነውም፤ ስለጉዳዩም አናውቅም እንዳትሉ ብቻ!!! እናንተማ!!! “ስማችሁ የለም” የሚለውን የወንድማችንን መጽሐፍ፣ “እኛን ለመንካት ነው” ብላችሁ ለግል ክብራችሁ ተጨንቃችሁ እንዳቄማችሁበትና እንደተፈራረማችሁበት ይታወቃል፡፡ በአንጻሩ ግን ለመድኃኔዓለም ክርስቶስ ክብር ግድ ሳይሰጣችሁ የኮሌጁን መምህር መጽሐፈ ኑፋቄ ለማውገዝ  ምነው ዝም አላችሁ?! አባቶቼ!!!

ይህም አካሔዳችሁ፣ ከሲኖዶሳዊነታችሁ ይልቅ ምን ያህል ግለሰባዊነታችሁ ላይ እንዳተኮረ ያንጸባርቃል፡፡ ስለ ዝናና ክብር የምትጨነቁ ከኾነ ከዓለማውያን በምን ተለያችሁ? በዓለማዊ ባለሥልጣናትና በአባቶች ሥልጣን መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የአባቶች ሥልጣን ባለቤቱና ሰጪው ነሺውም መንፈስ ቅዱስ  ነው፡፡ የዓለማዊ ባለሥልጣን ግን በምድራዊ ሥርዐት በፉክክር የሚመጣ ነው፡፡ በዓለማዊ ተቋማት ያለው ፉክክር፥ የደመወዝ፣ የሥልጣን፣ የምቾትና የይገባኛል ነው፡፡ ዓለማውያን ለሥልጣን ማግኘት የሚያደርጉት ፉክክር የሚያስነቅፋቸው አይደለም፤ ነገር ግን  በመንፈሳዊ መሪዎች መካከል ያለው የሥልጣን ፉክክር ያስነቅፋል ወይም ስለተሾሙለት ሕዝብ ሳይኾን ባሕር ማዶ  ተሻግሮ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚደረገው የምረጡኝ ዘመቻ አሁን ባለንበት በጳጳሳቱ ጉባኤ የተሰማ አይደለምን? ከዚህ የበለጠስ መንፈሳዊ ክስረት ምን አለ? “እነ አቡነ ደርበውስ” የተፈጠሩት አሁን ባለንበት የጳጳሳት አስተዳደር አይደለምን?

‘ደርበው’ ማለቴ የሀገሩን ውስጥ ሠርተው ሳይጨርሱ ለበጀቱና ማለትም ሁለት ሦስት ደመወዝ ለማግኘት ሲሉ ብቻ በፍቅረ ሢመት ተጠምደው ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን ሀገረ ስብከትና ሕዝብ እየተዉ ሌላ ሀገረ ስብከት የሚደርቡ፤ የእገሌ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ሓላፊ፤ የእገሌ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ፤ የእገሌ ተቋም ቦርድ ሰብሳቢ፤ የእገሌ ቤተ ክርስቲያን አሳራጊ የሚባሉ ደራቢና ተደራራቢ ጳጳሳትን ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ በበጀት እጥረት ሰበብ አንድ ሥራ አጥተው እየተራቡ ሁለት ሦስት ደመወዝ የሚያገኙ፤ የቤት ኪራይ የሌለባቸው፣ የኑሮ ውድነት የማያስጨንቃቸው፣ ሁሉን ትተው ጌታቸውን የተከተሉ ጳጳሳት፣ ሁለት ሦስት ደመወዝ መውሰዳቸው የጽድቅ ነው ትላላችሁ?

አንዳንድ አባቶችስ፣ “ሲኖዶሱ ጣልቃ እንዳይገባብኝ” እያሉ የምእመናን አቤቱታ እንዳይሰማ የሚያደርጉበት ዘመን አሁን አይደለምን? “ይህ የአባ እገሌ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው፤ ሲኖዶሱ አይመለከተውም፤” እየተባለ፣ አህጉረ ስብከት ከሲኖዶሳዊ አሠራር ውጭ ኾነው በጳጳሳቱ ይኹንታ ብቻ የሚተዳደሩበት የፍትሐ ነገሥት አንቀጽ አለን? ሕገ ቤተ ክርስቲያኑስ ቢኾን፣ ከመደበኛው ከፍትሐ ነገሥቱ የሕግ ትርጉም ጋራ ሊጋጭ ይገባዋልን? ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ሊሻሻል የሚችል ሲኾን፣ ፍትሐ ነገሥቱ ግን ቀዋሚ ሕግ አይደለምን?

እውነታው ይህ ከኾነ አባቶቼ፣ ሲኖዶሳችሁ፥ በሲኖዶሳዊ ጉባኤ ፍትሕ የተጓደለበትን ኹኔታ ሁሉ እየመረመረ ፍትሕ የምትሰጡበት ቅዱስ ጉባኤ መኾን ይገባዋል፡፡ ከዓመት እስከ ዓመት ያለው ቋሚ ሲኖዶስ መርምሮ ያላየውን አቤቱታቸውን፣ ምእመናን ለምልዓተ ጉባኤ ሲያቀርቡ፣ “አይ ይህን በቋሚ ሲኖዶስ እናየዋለን፤” እየተባለ ከዓመት እስከ ዓመት የሚንከባለሉ ችግሮችን ማየታችን ሲኖዶሱ  ፍትሕን ለመስጠት ያለውን ልዕልና በግለሰቦች ፍላጎት ሥር እንዳዋለው መረዳት እንችላለን፡፡ የአብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት እንዲያመራ ማድረጉ ነገ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ የተስተዋለ አይመስልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዓለማዊ አገዛዝ ፍርድ ቤት መዳኘት ስትጀምር ጅብ በቀደደው ውሻ ይገባል እንደሚባለው፣ ማኅበረ ምእመናን እየተፈራረሙ በዓለማዊ አገዛዝ ፍርድ ቤት እያስወሰኑ በቦርድ የሚመራ ቤተ ክርስቲያን የሚያቋቁሙበት ጊዜ ሩቅ አይኾንም፡፡ ይህ በኾነ ጊዜ፣ እገሌን ልሹምብህ እገሌን ልደርብብህ፤ ማለት ይቀራል፡፡ ያን ጊዜ የሚጮኸው ጩኸት የማይጠቅም ጩኸት ይኾናል፤አባቶቼ!!! መንፈሳዊ የኾነ የሃይማኖት መሪ መገለጫው፣ ትሕትናና ጥበብ እንጂ ዓምባገነንነትና አልሸነፍ ባይነት ሊኾን አይገባውም፡፡

በዓለማዊ ባለሥልጣናትና በመንፈሳዊ መሪዎች መካከል ያለው ልዩነት የቅድስና ሊኾን ይገባል እንጂ  የአልባሳት ልዩነት ብቻ ሊኾን ባልተገባው ነበር፡፡ ዓለማዊው ባለሥልጣን በቪ8 የሚሔድ ከኾነ መንፈሳዊው የሃይማኖት መሪ ደመና ጠቅሶ እንደ ሐዋርያት መንቀሳቀስ ነበረበት፡፡ ዓለማዊው መሪ በሱፍና በክራቫት ሲያሸበርቅ መንፈሳዊ የሃይማኖት መሪዎቻችን ደግሞ ባሸበረቁበት ልብሳቸው  ድውያንን በፈወሱ ነበር፡፡ ይህን በዘመናችን አላየንም፡፡ በዘመናችን ያየነው፣ እነ አቡኑ አለባበሳቸውን የመደብ ልዩነት ሲያደርጉት እንጂ ልብሳቸው የቅድስና መለያ ኾኖ እንደእነ ጳውሎስ ሕሙማንን ሲፈውሱበት፤ እንደ እነኤልሳዕ ባሕር ሲከፍሉበት አልተመለከትንም፡፡

አባቶቼ፣ ነገሩ እንዲህ ከኾነ፣ ከዓለማዊ ባለሥልጣናት በምን ተለያችሁ? በቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ችግሮች ተወያይታችሁ ደብዳቤ ከመለዋወጥ ባለፈ ውሳኔ የማትሰጡ ከኾነ እናንተ እነማን ናችሁ? አንዳንዶቻችሁ ፓትርያርክ መኾን ሳይቻላችሁ ሲቀር ለፓትርያርኩ እንደራሴ ልንሾምላቸው ይገባል የምትሉ፤ ለሥልጣን የምትፎካከሩ እናንተ እነማን ናችሁ? ፓትርያርኩስ ቢኾኑ ከእናንተ እንደ አንዱ አይደሉምን? ሁላችሁም እንደራሴ ያስፈልጋችኋል!!!

አባቶቼ ጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የማያሳስባችሁ ከኾነና ከማኅበረ ምእመናን ጋራ የምትገናኙበት መንገድ እየተቋረጠ ከሔደ ከዚህ በኋላ እርስ በራሳችሁ የምትመራረጡበትን የእስከ ዛሬውን አካሔድ በማስቀረት፥ ማኅበረ ምእመናኑ ያመኑበት፤ በዐይናቸው የሚያውቁት፤ በእጃቸው የዳሰሱት፣ በትምህርቱ የተማረኩበት፤ ለአመራሩና ውሳኔው የሚገዙለት፣ የሕዝብ ይኹንታና ተመጣጣኝ ውክልና የተሰጣቸው ሊቃውንትና ምሁራን አባቶች ተመልምለው የሚሳተፉበት ሕዝባዊ ሲኖዶስ ሊቋቋም ይገባል፡፡ አዎ እደግመዋለሁ፤ “የተቀደሰው” ጉባኤያችሁ ደስ አያሰኝምና ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ሀገር አንድነት ሲባል ሕዝባዊ ሲኖዶስሊቋቋም ይገባል!!!

“ኵሎ አመክሩ ወዘሠናየ አጽንዑ”

 

ገለቶማ !!!

Share.

About Author

Leave A Reply