ጉዞ አድዋ እና በህብረተሰቡ የተፈጠረው ብዥታ፡፡

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ባሕር ዳር፡ጥር 18/2011 ዓ.ም(አብመድ) ከአምስት ዓመት በፊት በአምስት ተጓዦች ነበር የተጀመረው ጉዞ አድዋ፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በነበሩት ዝክረ ጉዞ አድዋም 56 ተጓዦች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡ ዘንድሮ የሚከበረው 123ኛ የአድዋ ድል በዓል እንዳለፉት ጊዜያት በእግር ጉዞ ተጀምሯል፡፡
ከአለፉት ዓመታት በተለየ መንገድ የዘንድሮው ጉዞ አድዋ የተጓዦችና የጉዞ ቡድኖች በቁጥር ጨምሯል፡፡ 29 የተጓዥ አባላትን የያዘ አንድ የጉዞ አድዋ በጎ አድራጎት ማህበር እና 48 ተጓዦችን የያዘ ሌላ ቡድን በኬር ኢቨንት ኤንድ ኮምዩኒኬሽን ተዘጋጅቷል፡፡

በኢትዮጵ የዓይን ባንክ ድርጅት የአምባሳደርነት ተልዕኮ የተሰጠው የጉዞ አድዋ በጎ አድራጎት ማህበር መነሻውን በአዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል አድርጎ እና ‹‹ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት ለኢትዮጵያ!›› በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮውን ጉዞ አድዋ ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡

በሌላ በኩል በኬር ኢቨንት ኤንድ ኮሚዩኒኬሽን አዘጋጅነት የአድዋ ድልን ለመዘከር ከሃረር የተነሳ ሌላ የጉዞ ሁነት አዘጋጅ ቡድን አለ፡፡ ‹‹ትናንት በአድዋ የተከፈለልንን በማሰብ በመስዋትነት የተሰራችውን ሀገራችን በፍቅር ለመጠበቅ የሚያስችል መልዕክት ለትውልዱ ማድረስ!›› የሚል ዓላማ አንግበዋል፡፡
የዘንድሮው የአድዋ ድል የጉዞ በዓል ካለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት በተለየ መልኩ በሁለት የጉዞ ቡድኖች መካሄዱ በህዝብ ዘንድ ግርታ ፈጥሯል፡፡ የአድዋን ድል በዓል የመዘከር ዓላማ ያለው ጉዞ እና ተቀራራቢ ስያሜ መያዛቸው ግርታውን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡

ጉዞ አድዋ ከጉዞ ያለፈ ዓላማ እንዲኖረው እየሰራን ነው የሚለው የጉዞ አድዋ በጎ አድራጎት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ እሸቱ ማህበሩ ሌሎችን ታሪኮችን ጨምሮ ዓመቱን በሙሉ የሚሰራ በጎ አድራጎት እንዲኖር ጥረት እያደረግን ነው ይላል፡፡

የማህበሩ አስተባባሪ ጋዜጠኛ ሚኒሊክ ፋንታሁን እስካሁን በተካሄዱ ተከታታይ የአድዋ ጉዞዎች ሁሉንም የአድዋ ታሪኮች በአግባቡ እየዘከሩ አልነበረም፡፡ በዘንድሮው የጉዞ አድዋ በዓል አፄ ሚኒሊክ ወደ አድዋ ሲዘምቱ ባደሩባቸው ቦታዎች ሁሉ በማደር ታሪኩን ለማስታወስ እና የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልፆልናል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ላደረገላቸው የበጀት ድጋፍ ምስጋና ያቀረበው ማህበሩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስተር የድጋፍ ደብዳቤ ለመስጠት መዘግየቱን እና በአንዳንድ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ የተፈጠረው የማጥላላት ስራ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን በተለይም ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ተናግረዋል፡፡

ጉዞ አድዋን ለማካሄድ መንግስት ይፈቅድ ይሆን አይሆን ከሚል ጭንቀት ወጥተን በመንግስት የምንሸኝበት ጊዜ ላይ ደርሰናል የሚለው የጉዞ አድዋ ሁነት ዝግጅት አስተባባሪ አቶ ያሬድ ሹመቴ ምንም እንኳን ጉዞው አድካሚ እና ፈተና የበዛበት ቢሆንም የተከፈለልንን በማሰብ እንበረታለን ነው ያለው፡፡
የዘንድሮው የጉዞ አድዋ ዝግጅት በሁለት ቡድኖች በመደረጉ በህዝቡ ዘንድ ከፈጠረው ግርታ በተጨማሪም የህጋዊነት ጥያቄንም አስነስቷል፡፡

በጉዞ አድዋ በጎ አድራጎት ማህበር ስም ህጋዊ የሰውነት ምዝገባ ያለን የእኛ ማህበር ብቻ ነው የሚሉት የጉዞ አድዋ በጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ እሸቱ በዚህ ስም የሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ህጋዊነት አይኖረውም ይላሉ፡፡
በኬር ኢቨንት ኤንድ ኮምዩኒኬሽን ድርጅት የተዘጋጀው የጉዞ አድዋ አስተባባሪ አቶ ያሬድ ሹመቴ በበኩላቸው ትናንት አድዋ ላይ ድል ያደረጉት አባቶቻችን በአንድ አቅጣጫ አልሄዱም፡፡ መንገዳችን ቢለያይም መዳረሻችን አድዋ ነው፡፡ ከህጋዊነት ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ጥያቄ ግን እኛ ህጋዊ የሆነ እና በሚመለከተው አካል የተሰጠ ፈቃድ አለን ብለዋል፡፡

ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ የጠየቅናቸው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶር. ሂሩት ካሳው የህጋዊነት ጉዳይ ተቋማቸውን እንደማይመለከት ገልፀው፤ በየደረሱበት አካባቢ ህዝቡ ድጋፍ እና አቀባበል እንዲያደርግላቸው ግን ለሁለቱም የተጓዥ ቡድኖች የድጋፍ ደብዳቤ ሰጥተናል ብለዋል፡፡

አድዋ በሁለት ቡድኖች እና በውስን ተጓዦች ብቻ መወሰን የለበትም የሚሉት ሚኒስትሯ ተቋማቸው የተጓዦች ቁጥር በየጊዜው እያደገ እንዲሄድ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡ በጉዞ አድዋ የበጎ እድራጎት ማህበር የድጋፍ ደብዳቤ መዘግየትም በሰራተኞች የግልፀኝነት ችግር የተፈጠረ መዘግየት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

(የአማራ መገናኛ ብዙሀን)

Share.

About Author

Leave A Reply