ግልጽ ደብዳቤ ለተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር ዕብይ አህመድ – ከታምራት ይገዙ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የጥንት ቅርስ የሆነው የመጀመሪያው ዘመናዊ ሚኒሊክ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤትሊፈርስ ነው!

የህወሀት መንግስት በለስልጣኖች ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በአገራችን በኢትዮጵያ ካደረሱት ጥፋቶች አንዱ ታሪካዊ ቦታዎችንን ታሪካዊ የሆኑ ቅርሶችን አንድም ማጥፋት አሊያም ከአገር ማሸሽ ነበር:: ይህንን ዓይነት ክስተት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሃያ ሰባት አመት እንደ እሬት እያንገሸገሸው እንዲውጥ መደረጉን የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው:: ለአገርና ለህዝብ ያልሆነ አስከፊ አገዛዝ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የአማራና የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በከፈሉት የህይወት መሰዋትነት ለውጥ ሊመጣ ችሏል::

ለውጡ መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን የተገነዘባችሁ ቲም ለማ በሚባል ስብስብ ተሰባስባችሁ የነበራችሁና አሁንም ለውጡን እየመራችሁ ያላችሁ መሪዎቻችን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እናንተም ከህወሀት ነጻ ወጣችሁ:: ከዚህ በፊት በጹሁፌ ለማለት እንደፈለኩት ለውጥ መምጣቱን አውቃችሁ ለውጡን ለመቀበል ስለተዘጋጃቹና የኢትዮጵያ ህዝብ ያጣውንና የሚፈልገውን ስላወቃችሁ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” በማስከተልም “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ” በሚለውና በሚመስጠው አንደበታችሁ ምክንያት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችሁ ቆመ::

ከዛም ባለፈ እኛ የሽግግሩን ዘመን እናሻግራችሁ ስትሉት አሜን እንደ አንደበታችሁ ልባችሁ አንድ ከሆነ ይሁና ብሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚባል ደረጃ ደገፋችሁ እንደ አጀማመራችሁ ባይሆንም አሁንም የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ አላችሁ ብዪ በግሌ አምናለው::

ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዕብይ አህመድ በታሪካዊ ቅርጾች ላይ በተለይ የጥንት ቅርስ የሆነው የመጀመሪያው ዘመናዊ ሚኒሊክ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት ሊፈርስ ነው የሚለውን ዜና በርሶ የስልጣን ዘመን መስማት በቀላል አገላለጽ ያማል አዎን መላውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያሳምማል ብል ሃሰት አይሆንም:: ይህንን የሚኒሊክ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲፈርስ ትእዛዝ የሚሰጡት በእርሶ የተሾሙና አዲስ አበባን በአደራ ጠባቂነት በምክትል ከንቲባነት እያስተዳደሩት ያሉት አቶ ታከለ ኡማ ሲሆኑ እንደ እውነቱ ከሆነ አንዱ ባህላችን የነበረውና በህወሀት ዘመን አከርካሪውን የተሰበረው የባህል ቅርሳችን አደራ ተቀባይ የተቀበለውን አደራ በወጉ ይዞ የሚጠብቅ እንጂ አደራውን በይ አሊያም አፍራሽ እንዳልነበረ ነው::

ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዕብይ አህመድ አቶ ታከለ ሊወስዱት ያሰቡት ርምጃ በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ ቀዩን መስመር ማለፍ ነው ስለሆነም ይህ የአቶ ታከለ ኡማን የሚኒሊክ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት የማፍረስ እቅድ በኢትዮጵያዊነታችን የምናምነውን ሁሉ ለተቋውሞ የሚያስነሳ ስለ ሆነ ክቡር ጠ/ሚ አስቸኳይ እርምጃ ወስደው ይህ ትምህርት ቤት እንዳይፈርስ ሊታደጉት ይገባል ምክንያቱ ይህ ሚኒሊክ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት የአገራችን የኢትዮጵያ የታሪክ ቅርስ ነውና::

ይህንን የሚኒሊክ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያን ቅርሶች የማይታደጉ ጠ/ሚ ከሆኑ አርሶም ነፍሳቸውን ይማረውና እንደ ሞቹ ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዘናዊ በታሪክም በትውልድም ሲወቀሱ ይኖራሉ:: ከዛም በዘለለ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ “አፈ ቅቤ ሆደ ጩቤ“ የሚለውን የአባቶቻችንን ምሳላዊ አነጋገር እርሶ ላይ ይተርታል::

አንደ እውነቱ ከሆነ ሞቹ አቶ መለሰ አገራችንን ኢትዮጵያ ሲገዙ የነበረው “ይህቺ አገር“ እያሉ እንደነበረ እርሶም ያውቃሉ እኝህ ሰው በአካልና በመልክ ኢትዮጵያዊ በአስተሳሰባቸውና በልባቸው ግን የጀርመኑ ናዚ ነበሩ ብል ማጋነን አይሆንም:: ናዚ በአለማችን ላይ ያደረሰውን ጥፋት እርሶም ሆኑ መላው የአለም ህዝብ ያውቅዋልና መዘርዘር አይገባኝም::

የተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር ዕብይ አህመድ በኔ አስተሳሰብ እንደ ነ አቶ ታከለ ያሉ የቀድሞ የህወሀት ፖለቲካ ተጠማቂዎች አይነት ግለሰቦች ናቸው የእርሶን ተቀባይነት እየሸረሽሩ የሚገኙትና በጥንቃቄ ቢታዩ መልካም ይመስለኛል:: ክብር ጠ/ሚ ስለ አቶ ታከለ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ አብረው የተማሩ ወንድሞችና እህቶች ምስክርነታቸውን ሲሰጡ “የኢሃዴግ መራሹ ህወሀት መንግስት አንድ ወቅት ላይ ኦነግ ናቸው ብሎ ትምህርትታቸውን በወጉ እንዳይከታተሉ ከትምህርት ገበታቸው ያባረራቸውና ግፍ የተፈጸመባቸው ሰው ናቸው ይላሉ::”

እርሳቸውም በዛ ምክንያት አሁን ያሉበትን የኦሮም ድርጅት እንደተቀላቀሉ ይህንን ተከትሎ በተለያዩ የስራ ዘርፍ ተመድበው የሰሩ ሲሆን ይህንን ስልጣናቸውን ተጠቅመው መሬት በመሸጥ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው በተራቸው ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩ እንደ ነበር ሲተቹ ሰምቻለው:: ሲተቹ ሰምቻለው የምለው ቃል ይሰመርበት!

በኔ እምነት እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ናቸው የመጣውንና እየታየ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ እየሰሩ ያሉት ለምን ቢባል ለውጡን በማደናቀፍና እነርሱም ወደፊት ከተጠያቂነት ነጻ ለመውጣት የሚያደርጉት ታትክቲክ ይመስለኛል::

ክብር ጠ/ሚ ትላንት በነቂስ ወጥቶ ይደገፎት የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ”ሰውን ማመን ቀብሮ ነው” እንዳለችው ቀበሮ በጥረጣሬ እንዲመለከቶት ከሚያደርጉት በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ባለስልጣኖች ውስጥ አቶ ታከለ አንዱ ናቸው:: በኔ እምነት እንደ ነ አቶ ታከለ ያሉ ባለስልጣኖችን ቢቻል መሉ በሙሉ ከስልጣን አውርዶ እንደ ማንኛውም ህዝብ ታዛዥ ማደርግ ይገባል ባይ ነኝ ያን ግዜ እነርሱም የሰሩትን ክፉውንና ደጉን ለማወቅና ለማስታወል ግዜ ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ ::

የተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር ዕብይ አህመድ አጽኖት ሰጥቼ የምነግሮት ነገር የአገራችን የኢትዮጵያ ታሪካዊ የሆኑ ቦታዎችን ሆኑ ትምህርት ቤቶችን እርሶ በሾሟቸው አስፈራሽነት በርሶ የስልጣን ዘመን ሲፈርሱ አላየሁም አልሰማሁም ቢሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይታዘቦታል መጪው ትውልድም ይጠየፎታል በተጨማሪ የማንኛውም የሀይማኖት አባቶች ይቅር አይሎትም ምክንያቱም በርሶ የስልጣን ዘመን ሌላ የአገር ጥፋት እየተደረገ ነውና::

በተረፈ ግን ከዚህ በፊት በጹሁፌ እንደገለጽኩት የምችለውን በማድረግ በምክንያት እየደገፍኮት እገኛለው ወደፊትም በምችለው አቅም ከመደገፍ አልቦዝንም ነገር ግን የሚያስወቅሶት ነገር ካየሁና ያ ሊያስወቅሶት የሚገባ ከሆነ ከራሴ ጋር አውጥቼና አውርጄ ካመንኩበት ከመውቀስ አልመለስም የምወቅሶትም በአንደበቶት የተናገሩትን በሚችሉት አቅም እየተገበሩ በመሆኖትና ደጋፊዎት ስለሆንኩኝ ነው::

በመጨረሻም በዚቺ የአባቶቻችን አባባል ለዜሬው ልሰናበት “ከጠላትህ አንድ ግዜ ከወዳጅህ አስር ግዜ ተጠንቀቅ” ይላሉ!!!

አክባሪዎት ታምራት ይገዙ

Share.

About Author

Leave A Reply