ግልፅ መልእክት ለጃዋር መሀመድ፦ አንዳችንን ለማስቀደም ሁላችንም ወደሁዋላ አንቅር!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የተጫወትኸውን ጉልህ ሚና  1 2 3… ብሎ መዘርዘሩ ያንተንም የወዳጆቼንም ሰዓት ከማባከን የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አልወስድምና ማለፉን መረጥሁ።

ሆኖም የግድ ማንሳት ያለብኝ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበሰልህ፤ ወደ ላቀ ጉምቱ ፖለቲከኝነት እየተሸጋገርህ መሄድህንና ከምንም በላይ ተፅዕኖ ፈጣሪነትህን ስለምገነዘብ

ቀጣይ ጉዞህ በኢትዮጵያ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ባህላዊ ህይወት የሚኖረውን በአንተ አካሄድ ላይ የሚመሰረት

አሉታዊ ተግዳሮትና አዎንታዊ ፋይዳ ተገንዝበህ

በዚህ ሰዓት ተራርቀው የተፈራቀቁ ስሜቶችን ለማቀራረብ ታሪክ የሚመዘግበው መልካም አሻራህን እንድታሳርፍ የሚያስችል ቁመና ላይ ስላለህ በሁላችንም የልቡና ሰሌዳ የሚቀመጥ ታላቅ ቅርስ እንድታኖር እማፀናለሁ።

በኦሮሚያ ትግል ወቅት ዳታ ግንኙነት ሲጠፋ ከቦረናና ጉጂ ዞኖች ፈጣን መልእክቶችን በድፍረት እየተቀበልሁ አስተላልፍልህ በነበረ ወቅትም ስልኬን ተቀብለህ የተለዋወጥናቸው መልዕክቶች በትግሉ ወቅት ዓባይን በጭልፋ ቢሆንም የትስስራችን ማሳያ ከመሆኑ ሌላ

ሁልጊዜም ፍላጎታችን እኛ ሳንሆን ማህበረሰባችን የመሆኑ አመላካች ነው። ወዳጄ ይህ አንተ ፊት ለመቆም ድፍረት ባይሰጠኝም መነሻዬና መድረሻዬ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለልዩነት ነውና ጩኸቴ በዚህው ልክ መሆኑን ተረዳ።

ወደ ጭብጦቼ ልለፍ

ውድ ጃዋር፦

በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ታቅፈህ ለመታገል አለመወሰንህና ኢትዮጵያውያንን ለማቀራረብ እንደምትሰራ ማሳወቅህ የበለጠ እንድትገዝፍብኝ አድርጎሃል። በአንድ ድርጅት ብትታቀፍ ድርጅቱ አምባገነን ሆኖ ቢወጣ የክፋቱ አካል መሆን እንጂ ችግሩን አሳይቶ የማረም አቅምህ ይገደባልና። አሊያም የሽኩቻ አካል Faction መሪ ወደመሆን ዝቅታ ልትወርድ ትችላለህና።

ወዳጄ ታዲያ ይህ ከፍታህ ተጠብቆ የሚቆየው ብቻ ሳይሆን አብረውህ በምስሉ ላይ የምትመለከታቸው እናት የቄሮን የለውጥ ፍላጎትና የፋሺስቶችን ግፍ ተመልክተው፤ በዚያ ለእናቶች ጭምር ርህራሄ በሌለው የአግዓዚ ገዳይ ቡድን ፊት ዱላ አንስተው (ወጣቶቹን ለመታደግ አቅም ባይኖራቸውም) አብረው ለመሰዋት የጀገኑት ለውጥን ፍለጋ ነው።

አዎ በሀገራችን የለውጥ ፍላጎት ያልነበራቸውና አሁንም የሙጥኝ ብለው በትላንት ሰቆቃ ግፍ አረመኔያዊ ድርጊት እንድንቀጥል የሚሹት የሚከተሉት ቡድኖች ናቸው፦

፩ እንደ ደቡብ አፍሪካ (1948-1990) የቦሮች ማለትም የፈረንሳይና ደች ከዚሁ ጋር የብሪታኒያ በጥቅሉ ነጭ ዜጎች 86 እጅ % ምጣኔ ሀብቱን (ኢኮኖሚውን) ተቆጣጥረው

ጥቁሮች ተሸማቀው፣ የበዪ ተመልካች በመሆን፣ መብቶቻቸው በሙሉ ተጨፍልቀው የነበሩበትን አይነት ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጠረ ድባብ ማስቀጠል የሚሹ ግፈኞች ናቸው። እነዚህ ስብስቦች በዚች ሀገር የቁጥር እድገት መጥቷል በማለት ህንፃ የመቁጠርና የሚቆጥሩትን ረብጣ የማሳየት “የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶ እንዲሉ”

የደቡብ አፍሪካ ነጮች በዚያን ዘመን ከአፍሪካ አንደኛ የሆነ ምጣኔ ሀብት ገንብተው፤ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎችን ደርድረው፤ ቢሊዮኖች ዶላሮችን እያፈሱ የኖሩበት Vs.

በአንፃሩ የሀገሪቱ አብዛኛው ዜጋ (ጥቁሩ ወገን) የሚልሰውና የሚቀምሰው አጥቶ ተቀንሶ

ከነጭ ውሻ አንሶ እንደ ሰው ሳይቆጠር ነጭ ባየ ቁጥር ተሽቆጥቁጦ እንደኖረው ሁሉ (ህዝቡ አላልሁም የኢኮኖሚ ግዛቱ መስራቾች “ትግራይ ጉዳይ ገዳይ” ተብሎ

ጉዳይ ለማስፈፀም የትግርኛ ሙዚቃ በተንቀሳቃሽ ስልኮች/ሞባይል ለጥሪ አስጭኖ እስከማስደወል ተደርሶ እንደነበር)

በሀገራችንም ይህ ድባብ ሰፍኖ እንደቆየ አይካድም።

፪ እንደ ቅኝ ግዛት ዘመን ጥቂት የራሳችንን ወገን (ከሁሉም ክልሎች የተውጣጣ የጎበዝ አለቃ ድርጎና ፍርፋሪ እየተወረወረለት/ ፍርፋሪ ያልሁት ዋናዎቹ ከሚዘርፉት አወዳድሬ እንጂ የዳጎሰ ሀብት ነው) የጅብ አጋር በመፍጠር ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የነበሩ

፫ ፖለቲካውንም እነ መለስ አቦይ ስብሀት አባይ ፀሐዬ በረከት ስምዖንና የመሳሰሉት በአፋኝ የደህንነት መከላከያና አግኣዚ በማጠናከር (ሀጫሉ ሁንዴሳ “ሰው በላዎች ውስጣችንም አሉ”) እንዳለው ከህሊናቸው ሆዳቸው የሚገዝፍባቸውን ቅጥረኞች በመያዝ የቀጠሉና የዚህ ጥቅም ተጋሪ የሆኑ

፬ ከአማራ አፋርና ከሌሎች ክልሎች ግዛት እንደ ዳቦ እየቆረሱ የወሰዱና ያደሉ፤ ኤርምያስ ለገሰ ያጋለጠውን ካርታ የሰሩ፤ ራስ ደጀን ተራራን ጭምር የሰረቁ…

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሶማሊ ህዝብ ፍላጎት ባይሆንም በሁሉም አቅጣጫ (የኦሮሞን ትግል ሁለቱን ወንድማማቾች ለማፈን ሶማሊን የማስፋፋት አሻጥር ይከተሉ የነበሩ፤

ለምሳሌ፦ ነጌሌ ቦረናን ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡት የሶማሊ ተወላጅ የታዋቂው መሀመድ ኢጋል አባት ሲሆኑ

ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ቦረናን ወደ ኢትዮጵያ ሶማሊ ለማስገባት ህዝበ ውሳኔ ወይም Referendum ተካሂዶ ከተማዋ በእናቷ ኦሮሚያ ስር ብትቀጥልም፤ የቀድሞ 03 ቀበሌ ዳርቻዎች ወደ ሶማሊ ክልል ተካትተዋል። ይህንን ለማሳያ አነሳሁ እንጂ መላው ኦሮሚያ ላይ ይህንን ሸፍጥ ታያለህ) ሞያሌ ዑደትና አጎራባች ወረዳዎችን ታያለህ፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ/ኦሮሚያ፣ በወንዶ ገነት ከሲዳማ፣ አላጌን ከስልጢና አላባ፣ ጌዴኦን ከጉጂ … ሁሉም ስፍራ ኦሮሞን ከጎረቤቶቹ ወንድሞች የማጋጨት Time bomb

ከዚሁ መሳ ለመሳ የቦረና ጉጂ ዞንና የጉጂ ቦረና ዞን አከላለል ታልሞበት ቦረና ኦሮሞን ከአንድ እናት ልጅ ጉጂ ኦሮሞ ጋር የማጋጨት የክፋት ስልት ነው። በሂደት ጉጂ ዞን፣ ቦረና ዞን፣ ምዕራብ ጉጂ ዞን ሆኖ ወጣ። ይህ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቢሆንም ማህበረሰቡ የሺህ ዓመታት ያላንዳች ኮሽታ ችግሩን የሚፈታበት ስልት አለውና አያሳስበንም።

መነሻዬ የሰሜነኞቹ መስፋፋት፤ በዋናነት በተዘዋዋሪ የገዢዎችን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማረጋገጥ ማስቀጠል የሚሹ ወገኖች

፭ ስርዓቱ ያቆናጠጣቸውን ማህበራዊ ባህላዊና ግለሰባዊ የበላይነታቸውን ማስቀጠል የሚፈልጉ ሀይሎች

ሲሆኑ

ትግሉ ጥቅማቸውን ማስቀጠል በሚሹ ማፍያዎችና

መተንፈስ የጀመረውን አየር ላለማስነጠቅ በሚፋለመው ህዝብ መሀከል ነውና የቱንም ተጨማሪ ዋጋ ያስከፍለን ህዝብ ሁልጊዜም አሸናፊ መሆኑ አያጠያይቅም።

ሆኖም ማሸነፍ በራሱ ግብ አይደለም። ማሸነፍ ዘላቂ የሚሆነው የተከፈለው መስዋዕትነት ያለመድልዎና የእኔ የእኔ ሳይዘጋ የሚያድር የፉክክር ቤት ረክሶ ሳይሆን በአንድነት ተቀድሶና ተፈውሶ የኖርህበት የምዕራቡ ዓለም ያሰፈነው ገዢ አስተሳሰብ አሸንፎ ስንሰለጥን ነው።

ይህ እንዲሆን ከጃዋር እኛም ከጎንህ ቆመን ከነታማኝ በየነና ትንታግ አክቲቪስቶች ጋር በመሆን የሚከተለውን ለውጥ እንዲመጣ የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳለህ ብዬ አምናለሁ።

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ፍትሀዊ ጥቅም ሊከበር የሚችለው ሁልጊዜም የጦር አበጋዞች እንጂ የትኛውም ህዝብ የታሪክ በደል አካል እንዳልሆነ

ዛሬ ከሳሽና ተከሳሽ በዳይና ተበዳይ ፈራጅ ዳኛ፣ ሰጪና ችሮታ ተቀባይ እንደሌለና ከማንም ጋር የምናወራርደው ቂም በቀል ሌላ ዙር የጥፋት አዙሪት እንደሌለ ተገንዝበን፣ ላለፉት ዘመናት የሁላችንም ታላቅነቶች ቦታ ሰጥተን፣ በታሪካዊ መገፋፋት የሁላችንም የቀደመ ትውልድ በዚያ ዘመን አስተሳሰብ የሰራውን ስህተት ከዚያው ዘመን መነፅር ተውሰን ዐይተን፣ ቀጣዩ ጊዜ በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት (National Consensus) እና ብሔራዊ እርቅ (National Reconciliation) የምናመጣበት የይቅርታ የመደመር የምህረት የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን መስራት ይጠበቅብሃል።

ውድ ጃዋር፦

ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጎንለጎን

የኢኮኖሚ ዴሞክራሲ

የፖለቲካ ዴሞክራሲ

የማህበራዊ ዴሞክራሲ

ባህላዊ ዴሞክራሲ

የግለሰብ መብት

የጥቂቶች መብት

የቡድን መብት

የሀይማኖት የሴቶች የህፃናት የአረጋውያን የአካል ጉዳተኞች… መብቶች እጅግ ተጣጥመው

የአንድም ዜጋ መብት ሳይነካ ወገን በሀገሩ ተከብሮ ተገቢና የተመጣጠነ ምግብ አግኝቶ (በቀን ሶስት ጊዜ ቂጣ ይሁን ቆሎ በማይታወቅበት ሳይሆን) ወገን እንደ ዜጋ በአጭር ጊዜ የሚለወጥበት እድል አለን።

እንኳን ለእኛ ለዜጎቿ ለደተኞለች የምትበቃ ትልቅ ሀገር አለችን። ሳጠቃልል ለኦሮሞ ለአማራ ለትግራይ ለሲዳማ… ሳታዳላ አንተ የሁሉም ትሆን ዘንድ ወቅቱ ሰጥቶሃልና ሁሉንም በፍትሐዊነት እንድትታገል ጠይቃለሁ።

እኛ ማንም ኢትዮጵያዊነትን አይሸልመንምና ለሁሉም ለሚሆን ሁለንተናዊ ለውጥ ቁም። OMN በሂደት EMN እንደሚሆን አምናለሁ።

አንተ ከእንግዲህ የአንድ ወገን አይደለህም። ወደ ዓብይ ወደ ኢትዮጵያ ማማ ከፍታ ወደ ሰገነቱ ጫፍ ውጣ።

ሂድ አትቁም ገስግስ። አንተም ሌሎችም ተደምረን ትልቅ እንሁን። ኢትዮጵያ ትቅደም። አንዳችንን ለማስቀደም ሁላችንም ወደሁዋላ አንቅር።

አንዳችንን ለማግዘፍ ሁላችንም አንነስ።

በመጨረሻም ያንተ ገፅ ታላቅ ነውና ወሳኝ በሆኑ ፖለቲካዊ አንድምታዎች የአንድ ወገን መረጃ ስታገኝ ከሌላኛውም ሳታገናዝብ ለህዝብ አታቅርብ።

(ታዬ ቦጋለ አረጋ)

Share.

About Author

Leave A Reply