ግንቦት ወር በታሪክ ውስጥ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ግንቦት 1 ቀን 1849 ዓ.ም. ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል የሸዋ ንጉስ የነበሩ፤ ከሳህለ ሥላሴ ልጅ ከልዕልት ተናኘ ወርቅና ከደጅአዝማች ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ አባጉራች በ1849 ግንቦት 1 ቀን ጎላ ወረዳ ደርፎ ማሪያም በሚባል ስፍራ ተወለዱ፡፡

ግንቦት 9 ቀን 1860 ዓ.ም. የዓፄ ቴዎድሮስ ሚስት የልዑል አለማየሁ እናት እቴጌ ጥሩወርቅ በዚህ ቀን አረፉ::

ግንቦት 17 ቀን 1870 ዓ.ም. ዓፄ ዮሐንስ ዘ ኢትዮጵያ እና የሸዋው ንጉስ ምንሊክ በተገኙበት በወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ የተካሄደው የኃይማኖት ክርክር እልባት አገኘ፡፡

ግንቦት 15 ቀን 1907 ዓ.ም. አቤቱ እያሱ አባታቸውን ራስ ሚካኤልን ደሴ ላይ ንጉሠ ወሎ ወትግሬ ብለው አነገሷቸው፡፡

ግንቦት 25 ቀን 1921 ዓ.ም. የግብፅ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመጀመሪያዎቹን አራት ኢትዮጵያዊያንን፤ አቡነ አብርሐም የጎንደር እና የጎጃም፣ አቡነ ይስሃቅ የትግሬ እና የሠሜን፣ አቡነ ጴጥሮስ የወሎ እና የላስታ፣ አቡነ ሚካኤልን የኢሉባቡር እና የምዕራብ ኢትዮጵያ ጳጳሳት ሆነው በግብፃዊው ሊቀጳጳሳት አቡነ ቄርሎስ በካይሮ ላይ ተቀብተው ተሾሙ፡፡

ግንቦት 1 ቀን 1928 ዓ.ም. የኢጣልያ ንጉሥ ቪክቶር ዓማኑኤል ሳልሣዊ ከዚህ ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብና ግዛት የኢጣልያ አስተዳደር ስር መሆናቸውን ለዓለም መንግሥታት አሳወቁ፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ በኢጣልያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት እንደራሴ ማዕረግ በሚሾሙት ተወካዮችዋ አማካኝነት ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን እንደምታስተዳድር የሚገልፅ አዋጅ ይፋ አደረጉ፡፡

ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም. የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መሥራች ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ምኁር ዶክተር አሸናፊ ከበደ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ. ም. ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በስድሣ ዓመታቸው በዚሁ ቀን 1990 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ግንቦት 1 ቀን 1952 ዓ.ም. ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በአገራቸው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ኃይሎች መኖራቸውንና፤ እነዚህም ኃይሎች መንግሥታቸውን እንደተፈታተኑት በመግለፅ ከፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ግብፅ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ብሪታኒያ እና ዩጎዝላቪያ ዲፕሎማቲክ ሚሽን ተጠሪዎች ጋራ ተወያዩ፡፡ በስብሰባቸው ማግስት አምባሳደሮቹን ጠርቶ ለማነጋገር የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የተገደደው በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮች ላይ የባዕዳንን ጣልቃ ገብነት በብርቱ እንደሚቃወም እና በኢትዮጵያ ግዛትና ሉዐላዊነት ላይ ለሚሠነዘሩ ማንኛቸውም ጣልቃ ገብነቶችን ለመመከት ዝግጁ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማሳሰብ መሆኑን አሳወቁ፡፡

ግንቦት 9 ቀን 1952 ዓ.ም. የኤርትራ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትተዳደር ተስማምቶ የፈቀደውን ህገ-መንግሥት በመሻር የኤርትራን የራስ ገዝ አስተዳደር መንግሥት ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት መንግስት ጋር እንድትዋሃድ የሚያስችላትን ውሳኔ አፀደቀ፡፡

ግንቦት 24 ቀን1953 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ታሪክ እስከ አሁን ተወዳዳሪ ያላገኘ በሬክተር ሥኬል ስድሥት ነጥብ ሠባት የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ በሰሜን ሸዋ የምትገኘውን የማጀቴን ከተማ ሲደመስስ አጎራባችዋን ካራቆሬን ደግሞ ከመቶ እጅ አርባ አምስት ፐርሰንቱን አወደመ፡፡ በካራቆሬ በስተሠሜን ከአዲስ አበባ አስመራ የሚያገናኘው መንገድ ላይ ያሉ ድልድዮችን ከመጉዳቱ በላይ መቶ አስራ ሠባት ኪሎ ሜትር የድንጋይ ናዳ ጉዳት አድርሷል፡፡

ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም. የ32 የአፍሪካ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ ላይ ተሰብስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሠረቱ ፡፡

ግንቦት 1 ቀን 1963 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ሥርዐተ ሲመት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከናወነ፡፡ ግንቦት 15 ቀን 1963 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አደባባይ በመውጣት በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ከማሠማታቸው በተጨማሪ የአንበሳ ከተማ አውቶብሶችና የመንግሥት ንብረቶችን አወደሙ፡፡ ይህንንም ተከትሎ አስር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወሠነ ጊዜ እንዲዘጉ ተደረገ፡፡

ግንቦት 15 ቀን 1966 ዓ.ም. የኤርትራ ነፃነት ግንባር አባላት ጊንዳ ውስጥ በሉተራን ሚሲዬን ሆስፒታል ውስጥ የሚሠራ ኢጣልያዊ ዶክተርን ለመጥለፍ ሞከሩ፤ በዚህ እንቅስቃሴያቸው አንዲት አስታማሚ ኢጣልያዊት ነርስ ተገደለች፡፡

ግንቦት 15 ቀን 1966 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን መንግሥት የሚኒስትሮች ለውጥን ይፋ አደረገ፡፡ በዚህም መሠረት የአገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩትን ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴን ወደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ማዘዋወሩን አሳወቀ፡፡

ግንቦት 23 ቀን 1966 ዓ.ም. የየካቲቱን ህዝባዊ ዓመፅን ተከትሎ በንጉሠ ነገሥቱ ይሁንታ የተቋቋመው የመርማሪ ኮሚሽን ሥራውን የሚሠራበት ህግና ማዕቀፍ በህዝብ እንደራሴዎቹ ምክር ቤት ፀደቀ፡፡

ግንቦት 17 ቀን 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ የነበሩትን አቶ ተስፋዬ ቡሽን የጠቅላይ ግዛቱ ህዝብ ከሥልጣናቸው አባሮ አስወጣቸው፡፡

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም. በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም የሚመራውን የኢሕድሪ መንግሥት ከሥልጣን ለማሥወገድ በአገሪቱ ከፍተኛ የጦር አዛዦች የተቀነባበረ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተካሄደ፡፡ መፈንቅለ መንግስቱ በኮሎኔል መንግስቱ ታማኝ ወታደሮች ጥረት የከሸፈ ሲሆን በመንግሥት ግልበጣ ኩዴታው ላይ የተሳተፉትን የጦር አዛዦች በሙሉ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዕዛዝ በሞት እንዲቀጡ ተደረገ፡፡

ግንቦት 7 ቀን 1983 ዓ.ም. ህዝባዊ ግንባር ለፍትሕለዴሞክራሲ (ሻዕቢያ) መላዋን ኤርትራ በመቆጣጠር በኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት መመሥረቱን አሳወቀ፡፡ ከዚህ ዕለት አንስቶ የእሥራኤል መንግሥት በኢትዮጵያ ይገኙ የነበሩትን 14 ሺህ 325 ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን በ36 ሠዓት ውስጥ በ44 የእሥራኤል አውሮፕላኖች አጓጉዛ ወሰደች፡፡

ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም. የኢሕድሪ ፕሬዝዳንት፤ የኢሠፓ ዋና ጸሐፊ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አገር ጥለው በመኮብለል ወደ ዙምባብዌ ተሰደዱ፡፡

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የኢህአዴግ ጦር መላውን የኢትዮጵያ ግዛት መቆጣጠሩን አሳወቀ፡፡ በወቅቱ የኢህአዴግ ጦር ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ እንዲገባ የወሠኑትና በለንደን የሰላም ድርድሩን ይመሩ የነበሩት የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ኸርመን ኮኸንን ፈቃድ ተከትሎ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡ የጊዜያዊ መንግሥቱ ፕሬዘዳንት መለስ ዜናዊም ቀናት ሳይቆዩ አዲስ አበባ ገቡ፡፡

ግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም. በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት ጦር በሰሜን ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት የግዛት ድንበርን በመጣስ ወረራ አካሄደ፡፡ በዕለቱ የተጀመረው የሁለቱ አገራት የድንበር ውዝግብ አሁንም መፍትሄ ሳያገኝ በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply