ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ለእስልምና እምነት ተከታዮች መልእክት አስተላለፉ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

“ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለተቀደሰው የረመዳን ጾም በሰላም  አደረሳችሁ፤ ረመዳን ከሪም፡፡                                                         ይህ ወር የተለየ ወር ነው፡፡ የልዩነቱ ሚስጥር ደግሞ ከሰላም፣ ከፍቅር፣ ከመረዳዳት፣ ከአንድነት፣ ከእዝነት ከመሰጠት እና ከሌሎች በርካታ መንፈሳዊ ትሩፋቶች ጋር የተዛመደ ወር ከመሆኑ ጋር ስለሚሰናሰል የረመዳን ታላቅነት እና ይዞልን የሚመጣውም በረከት ብዙ ነው፡፡ ሰው ከስጋዊው ጠንካራ ህልውና ቢበልጥ እንጂ በማያንስ የአስፈላጊነት ደረጃ መንፈሳዊ ስብእና ወይም ከነፍስ የሆነ ብጽእና ያስፈልገዋል፡፡

ይህ ሲሆን ደግሞ በተለያዩ ባህሎች እና የሀይማኖት መሰረቶች ውስጥ ያሉ መልካም እሴቶች በኑሯችን እና በዘወትራዊው የህይወት ልምምዳችን ውስጥ ተገቢውን ስፍራ እንዲይዙ ይሆናል፡፡ ይህን ለማድረግ እድል ከሚሰጡን መንፈሳዊ ተግባራት ውስጥ አንዱ የረመዳን ጾም ነው፡፡
ይህ ወር እንደ ሰላም ወርነቱ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት- ስለ ልጆችዋም ሁሌያዊ አንድነት እና ብልጽግና ተግታችሁ የምትጸልዩበት ወር እንደሚሆን በጽኑ አምናለሁ፡፡ ጾሙ ወደ ውስጣችን የምንመለከትበት- ከራሳችን ጋርም ታርቀን ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት ወቅት በመሆኑ ለሀገር እና ለህዝብ የሚበጅ ሀሳብ እና በተጨባጭም ወደ መሬት የሚወርድ ተግባር እንድንከውንበት እድል ይሰጠናል፡፡

በመሆኑም በዚህ የጾም ወር መላው ሀገራችን ሰላም እንዲሆን እና ህዝባችንም በሰላም ተዋዶ – በፍቅርም ተዋህዶ የመኖር የዘመናት ታሪኩ ዛሬም ነገም- ወደ ፊትም አብሮት ይዘልቅ ዘንድ እንደ ሁል ጊዜው በጸሎት- ዱአችሁ እንድትማጸኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በመጨረሻም ታላቁ የጾም ወር ደግ ደጋችን በዝቶ ክፉ ክፉው የሚቀነስበት የሰላም፣ የአንድነት፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የሀሴት እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን እየገለጽኩ አሁንም በድጋሚ ረመዳን ከሪም ልላችሁ እወዳለሁ፡፡”

ዶ/ር ዓቢይአህመድ
የኢፌድሪጠቅላይሚኒስትር

Share.

About Author

Leave A Reply