ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የኤርትራ ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ያካሄዱትን የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ጠዋት ነበር አስመራ የገቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አስመራ ሲደርሱም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የአስመራ ከተማ ነዋሪ ኤርትራውያን ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ቆይታቸውም ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ትናንት ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ሁለቱ ሃገራት አቋርጠውት የነበረውን ግንኙነት ዳግም ለመጀመርና፥ የሁለቱ ሃገራት አየር መንገዶችም መደበኛ በረራ እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ከዚህ ባለፈም በወደብ ልማት በጋራ በመስራት የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩም ተስማምተዋል።

ከዚህ ባለፈም በሁለቱ ሃገራት መካከል ተቋርጦ የነበረው መደበኛ ስልክም ከትናንት ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራው ተመልሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ሁለቱ ሃገራት በድንበር ሳቢያ ግጭት ከገቡ በኋላ አስመራን የረገጡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ ሆነዋል።

Share.

About Author

Leave A Reply