ጠ/ሚ አብይ አህመድ በአጼ ሀይለስላሴ ሀውልት ጀርባ የራሱን ሀውልት አቆመ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም የሚል አባባል አለ። የኢህአዴግ መንግስት የኢትዮጵያውያንን ያለፈ ታሪክ በሙሉ በጥቁር ቀለም ቀብቶ፣ ለትውልድ እንዳይተላለፍ ደግሞ በስርአተ ትምህርቱም፣ በፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳውም እያደረገ ለሀገር ልማትና እድገት ለመስራት ካቀደው እጥፍ በላይ በታሪክ ማጥፋት ተጠምዶ ፪፯ አመታትን ዘልቆ አሁን ወደ አንድ ጥግ ተሸጉጦ ይገኛል።

ኢህአዴግ ታሪክን ከመፍራቱ የተነሳና የራሱን ቁንጽል የቡድን ታሪክ ለማግነን ካለው ፍላጎትና የቁም ቅዠት በመነሳት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው የቀድሞ መሪዎች መካከል የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉስ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ናቸው። በሀገር ውስጥ ይቅርና እኚህ ታሪክ መቼም ሊዜነጋቸው የማይችለውን ንጉስ በአፍሪካ ህብረት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አፍሪካውያን እንኳ እንዳያስታውሷቸው ተግቶ በመስራት በርካታ የቀድሞ አፍሪካዊ መሪዎችና ለህብረቱ አስተዋጾ ያደረጉ ሲታሰቡና ሀውልታቸው ሲቆም ስውር ሴራ ሲሰራ ቆይቷል።

ፖለቲካ አላፊ ነው። ምንም አይነት አስተሳሰብ ዘላለማዊ ቅቡልነት ሊኖረው አይችልም። የትናንቱ ምርጥ አታጋይ ፖለቲካ ዘንድሮ የበሰበሰ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ትውልድ በመጣና በሄደ ቁጥር ለሚለወጥ የፖለቲካ አስተሳሰብ መሰረታዊ ነገሮችን ለመናድ መሞከር ትርፉ ትዝብትና የመልስ ምቱ በራስ ላይ ጥላቻን መዝራት ይሆናል። የትኛውም መሪ መቶ ከመቶ ሊወደድና ሊሞገስ አይችልም። በተወሰነ መልኩ ወደስልጣን ሲመጣ፣ ስልጣን ላይ ሲሆንና ከስልጣን ሲወርድ የሚያጠፋቸው ነገሮች በርካታ ናቸው። ይሁን እንጂ ያለፈ የሀገር ታሪክ አካል ነውና የሚበልጠውን መልካም ነገሮቹን በማውጣት ለዛሬው መማሪያ ማድረግ ተገቢ ነው።

በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ያንን ሁሉ ሴራና ተንኮል ተሻግረው የአጼ ሀይለስላሴ ሀውልት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እንዲቆም ማድረጋቸው ለእርሳቸው ለራሳቸውም አንድ ገድል ሆኖ የሚጻፍላቸው ይሆናል። እሳቸው እንደተናገሩትም ሀውልቱ የንጉሱ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት እና ነጻነት ላደረገችው ግንባር ቀደም ተሳትፎ እውቅና እና መታሰቢያ ነው።

ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያም እንዲሁ ንጉሱ ለሀገራችን ባደረጉት ዘመናዊ አስተዳደርና ዘመናዊ ትምህርት፣ የማይዘነጋ አለማቀፋዊ ዲፕሎማሲና ቅቡልነት፣ እንዲሁም በርካታ መልካም ነገሮች ታሳቢ ተደርገው በስማቸው አንድ ሁነኛ መዘከሪያ ብታቆምላቸው በተገባ ነበር።

አጼ ሀይለስላሴ በበርካታ አፍሪካ ሀገራት ሀውልቶ ቆሞላቸዋል፣ ትምህርት ቤቶችና ጎዳናዎች በስማቸው ተሰይመዋል። በአጼ ሀይለስላሴ ብዙ መታሰቢያዎች አፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያውያን የትናንቱ ታሪክ ላይ ያውም ክፉ ኩነቶቹ ላይ ብቻ ተኝተን መልካም ነገሮችን ነቅሰን አውጥተን ይህንኑ ለመድገም ምናልባት እንደ አቢይ አህመድ አይነት ቀና አሳቢ መሪ እንዲሁም ቀና ተቻቻይ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያስፈልገናል። ያም ሆኖ አብይ አህመድ በአጼ ሀይለስላሴ የአፍሪካ ህበረት ሀውልት የራሱንም ሀውልት ማቆሙን ኢትዮጵያውያን መዝግበዋል።

Share.

About Author

Leave A Reply