ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ የጅቡቲ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢፌዴሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጅቡቲ ለሁለት ቀናት ያደረጉትን የመጀመሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ቀናት ጉብኝታቸው ትኩረት ሰጥተው ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ውህደትን እውን ለማድረግ መስማማታቸው ዋነኛው ነው፡፡

በዚህም ሀገራቱ በጋራ የሚያስተዳድሩት ወደብ ለማልማት በሐሳብ ደረጃ ተስማምተዋል፡፡

ይህ አዲስ በጋራ ይመሰረታል ተብሎ የታቀደው ወደብ ከኪራይ ነጻ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

እንዲሁም የጂቡቲ መንግስት በቴሌኮምና በሌሎች ልማቶች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ቢሰሩ ትስስሩን የበለጠ ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ተዛማች ተቋማት ጋር የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በማቋቋም ዝርዝር ሀሳብ እንዲያቀርቡ መመሪያ ተሰጥቷዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ ባሰሙት ንግግርም የኢትዮጵያንና ጅቡቲን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የሀገራቱ የህዝብ ተወካዮች ሚና መጉላት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት፣ አንድነትና የሚያመሳስሏቸውን የማንነትና የኑሮ ዘይቤዎችን አንስተዋል።

ከዚህ በፊት የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት የፓርላማ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

ከዚህም በላይ የተሻለ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ትብብር እንዲኖር “የፓርላማ አባላት ተቀራርበው ልምድ እየተለዋወጡ መስራት አለባቸው” ብለዋል።

የሁለቱን ሀገራት ፖሊሲ ማጣጣም ላይ የበለጠ መስራት እንደሚገባ በመግለጽ ለሀገራቱ ህዝቦች ጥቅም ሲባል ይህ ሐሳብ በተግባር እውን እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

(ፋና)

Share.

About Author

Leave A Reply