“ጣልቃ አይግቡብንም፤ እኛም በእነሱ ጣልቃ አንገባም” አቶ ጌታቸው ረዳ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ሀገር ግንባታ ላይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ የተናገሩት ትክክል አይደለም ሲሉ የህወሀት ቃል አቀባይ ገለጹ። የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊና ቃለቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለኢሳት እንደገለጹት የወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ንግግር በቀጥታ የትግራይ ክልል የተመለከተ ለመሆኑ ማረጋገጥ ባልችልም ከሆነ ግን እንደዚያ የማለት መብት የላቸውም ብለዋል።

ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ ያለማክበር ሁኔታ ይስተዋላል በሚል የፍትህ ሳምንትን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በሀገር ግንባታ ወቅት ህግን ለማስከበር መወሰድ ያለበት እርምጃ ሁሉ ይወሰዳል ማለታቸው ይታወሳል። በዚህም የአሜሪካንን ምሳሌ በመጥቀስ ለህግ ማስከበር እምቢተኛ ወደ ሆነ ግዛት የአሜሪካን ፕሬዝዳንት የነበሩት አይዘንሀወር ሰራዊት ልከው ህግን ማስከበር መቻላቸውን መጥቀሳቸው በተለይ በትግራይ ተወላጅ በሆኑ አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች ተቃውሞን አስነስቷል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ የትግራይን ክልል በስም ባይጠቅሱም ጉዳዩ ከቀድሞ የደህንነት መስሪያ ሃላፊ ከነበሩትና በፍርድ ቤት ያልቀረቡትን አቶ ጌታቸው አሰፋን የተመለከተ ሊሆን እንደሚችል የትግራይ የመብት ተሟጋቾች በመግለጽ ላይ ናቸው። በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌብነት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸውን የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ እንደማይሰጥ የትግራይ ክልል መንግስት ማስታወቁ የፌደራል መንግስቱን ህግን የማስከበር አቅሙ ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው ይነገራል።

የወ/ሮ መዓዛን ንግግር በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊና ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ትግራይ ክልል ስለማለታቸው ባላውቅም የማለት መብት ግን የላቸውም። በፍርድ ቤት ጣልቃ እንደማንገባ ሁሉ እሳቸውም በእኛ ጉዳይ ባይገቡ ይመረጣል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ሰሞኑን የተደረገውን የፍትህ ሳምንት ከህግ ጉዳይ ይልቅ የፖለቲካ መድረክ እንዲሆን ተደርጓል ሲል ቅሬታ አቅርቧል። የቢሮው ሃላፊ አቶ አማኑዔል አሰፋ ለድምጸ ወያኔ በሰጡት ቃለመጥይቅ እንደገለጹት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለልተኛ አልሆነም ብለዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወሮ መዓዛ አሸናፊ ን በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።(ምንጭ:- ኢሳት)

Share.

About Author

Leave A Reply