‹‹ጥቃቱ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጉዳት ነው፡፡›› የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች፡፡

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2011ዓ.ም (አብመድ) ከተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ወደተሳሳቱ ድምዳሜዎች እንዳያመሩ እና የሀገር ግንባታ ጥረቱ እንቅፋት እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው አንዳንድ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ‹‹ጥቃቱ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጉዳት ነው›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት ክልሉ ውስጥ በየወቅቱ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች የዚህ አካል ሊሆኑ ስለሚችሉ መንግሥት እና ሕዝብ በተረጋጋ መንፈስ ሊያጠኗቸው የሚገባበት ወሳኝ ወቅት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

በጥቃቱ ለሕዝብ እና ለሕግ ተገዥነት ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ሐዘናቸው ጥልቅ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፤ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ወደተሳሳቱ ድምዳሜዎች እንዳያመሩ እና በሀገር ግንባታ ጥረቱ ላይ እንቅፋት እንዳይሆኑ ኅብረተሰቡ ከስሜት ነፃ ሆኖ ሊጠብቅ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎችና እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ላይ የደረሰውን ግድያ መንግሥት የጥፋቶች ሁሉ ማብቂያ አድርጎ ሕግ የማስከበር ሥራውን አንድ ወጥ በሆነ ተቋም እንዲመራውም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት በላከው የሐዘን መግለጫ ደግሞ በአማራ ከልል እና በፌዴራል ደረጃ በተፈፀመው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሕይወታቸውን ያጡ መሪዎች እና ንፁኃን የሕግ አስከባሪዎች ሁሉን ያስደነገጠ እንደሆነ አመላክቷል፡፡ አደጋው የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ በቁጭት አጠናክረው ግባቸውን እንዲያሳኩ የሚያደርግ እንጂ የፀረ ሠላም ኃይሎች ፍላጎት እንዲሳካ በር የሚከፍትም እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡ ሕዝቡ ከተለያዩ ምንጮች በሚሰነዘሩ ግምቶች የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ ደርሶ ብሶት እንዳይፈጥር ወቅቱን በተረጋጋ እና በሰከነ መንገድ ማለፍ እንደሚኖርበትም ተጠቋሟል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply