ጥፋት በጥፋት አይታረምም !! ከተፈናቃዮች ጋር የተወያዩ አባገዳዎች

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ከቡኖ በደሌ የተፈናቀሉትን የአማራ ተወላጆች ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሠራ ነው፡፡

 

ትናንት ሐምሌ 12/2010 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የቤቶችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ግርማ አማንቴ የተመራው አባ ገዳ የልዑክን ቡድን በባህርዳር ከተማ ከተፈናቃዮች ጋር ተወያይቷል፡፡

‹‹ዛሬ የመጣነዉ እናንተን ለማወያየት ሳይሆን ወደ ቀያችሁ ይዘናችሁ ለመመለስ ነው›› ያሉት ዶክተር ግርማ አማንቴ ተፈናቅለው ችግር ላይ የወደቁት የአማራ ተወላጆች የተፈጸመባቸውን በደል በይቅርታ አልፈው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ ጠይቀዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ደግሞ ችግሩ የቆየና ተደጋጋሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ንብረታቸውን ማጣታቸውን ነው ያስረዱት፡፡አሁንም ወደ ነበሩበት ቢመለሱ ተመሳሳይ ጉዳት ይደረስብናል የሚል ስጋት አላቸው፡፡

ችግር እየፈጠሩባቸው ያሉት ህብረተሰቡ ሳይሆን የመንግስት አካላት መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ እናም “ወደ ቀያችን ለመመለስ ዋስትና የለንም” ብለዋል፡፡

የቡኖ በደሌ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ለጥይበሉ ሞቱማ በበኩላቸው ተፈናቃዮቹን ለመመለስ ከህብረተሰቡ ጋር ሌት ከቀን ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረው ‹‹ህብረተሰቡ ወገኖቻችን ይመለሱልን ብሎናል ››የሚል አስተያየት ሠንዝረዋል ፡፡

በፀጥታው ረገድም መንግስት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ አስረድተው ዘመኑ የመቃቃር ሳይሆን የመዋደድ ዘመን በመሆኑ ወደ ቀያችሁ ተመለሱ ብለዋል፡፡

ከልዑክ ቡድኑ አባላት መካከል አባገዳ ተሾመ በቀለ ” በኦሮሞ ባህል ጥፋት በጥፋት አይታረምም” ስለዚህ ያለፈውን ሁሉ ነገር ትታችሁ ወደ ቀያችሁ ተመለሱ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለመፈናቀል ምክንያት በሆኑ አመራሮች ላይ የክልሉ መንግስት እርምጃ መወሰዱም ተነግሯቸዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ደግሞ ተፈናቃዮቹ እስኪቋቋሙ ድረስ የሁለቱም ክልል መንግስታት ከጎናቸው እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ሰኔ 8 /2010 ዓ.ም. የቡኖ በደሌ ዞን አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ.ቤት ኃላፊ ከተፈናቃዮች ጋር መወያየታቸዉ ይታወሳል፡፡                                                                                                                                                                                                                          ምንጭ  አማራ ማስ ሚዲያ

Share.

About Author

Leave A Reply