ፍርድ ቤቱ አቶ ኢሳያስ ዳኘው በ200 መቶ ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወሰነ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ፍርድ ቤቱ አቶ ኢሳያስ ዳኘው በ200 መቶ ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወሰነ።

ግለሰቡ በኢትዮ ቴሌኮም የኤን ጂ ፒ ኦ ዳይሬክተር የነበሩትና ለሜቴክ የተሰጠን ውል በማሻሻልና ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል በከባድ የሙስና ወንጀል ነበር የተጠረጠሩት።

መርማሪ ፖሊስ በተፈቀደለት የሰባት ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ከፕሮጀክቱ ጋር የተያያዘ የኦዲት ሪፖርት እንዲያዘጋጅልን ጠይቀን እንዳልጨረሱልን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈውልናል ብሏል።

ከዚህ ባለፈም ከሳይት ርክክብ ጋር በተያያዘ ከአዲስ አበባ ውጭ የምንቀበለውን የምስክርነት ቃል በተሰጠን ጊዜ ውስጥ መቀበል ባለመቻላችን ተጨማሪ የ14 ቀን የማጣሪያ ጊዜ ይፈቀድልን ብሎ ጠይቆም ነበር።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የወንጀል ችሎትም የቴሌ ታወር ተከላ ፕሮጀክቱ ትልቅ እንደመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም የኦዲት ሪፖርት አላሰራም ገና እያሰራ ነው መባሉ አሳማኝ ምክንያት አለመሆኑን ጠቅሷል።

ከአዲስ አበባ ውጭ የምንቀበለው የምስክርነት ቃል አለ በሚል የተገለጸውም ቢሆን በተሰጣችሁ ጊዜ ውስጥ የምስክርነት ቃሉን መቀበል ትችሉ ነበር በማለት መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ሳይፈቅድ ቀርቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች መርማሪ ፖሊስ ስራውን በተገቢ ሁኔታ እየሰራ አይደለም፤ እስካሁን የተፈቀደው ቀን ይበቃል ተጠርጣሪው በዋስ ወጥተው እንዲከራከሩ ይፈቀድልን በሚል ያቀረቡትን ጥያቄ ችሎቱ ተቀብሎ ተጠርጣሪው በዋስ እንዲወጡ ወስኗል።

የተጠርጣሪውን የግል ሁኔታ ከግምት በማስገባትም በሁለት መቶ ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ችሎቱ ወስኗል፤ ከዚህ ባለፈም ተጠርጣሪው ከሃገር እንዳይወጡ እግድ ተላልፎባቸዋል።

መርማሪ ፖሊስም ይግባኝ ስለምጠይቅ ዋስትናው ይታገድልኝ ሲል ጠይቆ ችሎቱ አቤቱታውን በጽሁፍ ማመልከቻ እንዲያስገባ አዟል።

FBC

Share.

About Author

Leave A Reply