ፍርድ ቤቱ የቀድሞ የሜቴክ አመራሮችን ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ አደረገ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ከመርከብ ግዥ ጋር በተያዘዘ በቀድሞ የሜቴክ አመራሮች ላይ የቀረበ የክስ መቃወሚያ ውድቅ አደረገ፡፡

የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውና ምክትል የነበሩት ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤልን ጨምሮ 14 ተከሳሾችን የክስ መዝገብ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የተከሰሾችን መቃወሚያ ውድቅ አድረጓል።

የኮርፖሬሽኑን የግዥ መመሪያ በመጣስ ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ባህራና ትራንዚት ሎጅስቲክስ አገልግሎት ከገዛቸው መርከቦች ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎቹ በመንግስትና ህዝብ ሀብት ላይ ከ544 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አቃቤ ህግ በክሱ አመላክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ ላይ ተቃውሟቸውን ያቀረቡ ሲሆን÷ አቃቤ ህግ በክሱ ያቀረበው ፍሬ ነገር በማስረጃ መጣራት እንዳለበት በመግለጽ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።

ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውና ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም በወንጀል ድርጊት በመሳተፍ የመንግስትን አሰራር በማያመች አኳሃን በመምራት አቃቤ ህግ ባቀርባቸው ሁለት ክሶች ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ በመጥቀሱ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል።

በአንደኛው ክስ የተጠቀስን ፍሬ ነገር በመከፋፈል በሌላ ክስ ላይ መጠቀሙ ተገቢ ባለመሆኑ ክሱን አሻሽሎ ወይንም በአንድ አጠቃሎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል።

አቃቤ ህግ የተሻሻለውን ክስ ለማቅርብም ችሎቱ ለመጋቢት 13፣ 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply