ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ ዲ. ዳንኤል ክብረት ባሳተመው ‹ኢትዮጵያዊ ሱራፊ› አዲሱ መጽሀፍ የሰጡት ትንታኔ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ይህ መጽሐፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ አባት የነበሩትን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን የሕይወት ታሪክ በማስረጃ ላይ ተደግፎ ያቀርባል፤ ለክርስትና መስፋፋት ያደረጉትን ተጋድሎ በስፋት ይተርካል፡፡

ዘመናትን ውጣ ውረድ ተቋቁመው እስከ ዛሬ የመጡትን በግእዝ የተጻፉ ሰነዶች በሙሉ በማየት፣ ሀገራችንን ለመጎብኘት ከውጭ ሀገር በመጡ ሀገር አሳሾች የታተሙትን ድርሳናት አሟጦ በመመርመር፣ ከአዲስ አበባ እስከ ደብረ ዳሞ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ኢየሩሳሌም በመሄድ አባቶችን በማነጋገር ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያለውን ትውፊት በመሰብሰብ፣ በተለያዩ የብራና መጻሕፍት ውስጥ እና በአያሌ አድባራት እና ገዳማት ግድግዳ ላይ ከ15ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የተሣሉትን ሥዕሎች በጥልቀት በመገምገም፣ የታሪክ ሊቃውንት በጻድቁ ላይ የጻፉትን በስፋት በመዳሰስ ይህንን መጽሐፍ አዘጋጅቶ አቅርቦልናል፤ በመጽሐፉ ውስጥ ብቻ ከመቶ ስድሳ ስምንት ያላነሱ ሥዕሎች ተካተዋል፤ ይህም ለዚህ ሕይወት ታሪክ ተጨማሪ ዋጋ ይሰጠዋል፤ እስካሁን በታሪክ ሊቃውንት የልተመረመሩ ወደ ሃያ የሚሆኑ ገድላትን ማግኘትና ማጣቀስ ችሏል፡፡

ደራሲው የሚያቀርበውን እያንዳንዱን ተረክ በማስረጃ እያስደገፈ፣ ይህንንም ማስረጃውን በግልጽ በግርጌ ማስታወሻ እያስቀመጠ፣ የቅዱሱን የሕይወት ታሪክ አቅርቦልናል፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሰሜን ከኤርትራ እና ከትግራይ ጀምሮ እስከ ደቡቡ፣ ምዕራቡ እና ምሥራቁ የሀገራችን ጫፍ ድረስ በስማቸው በተሰየመ ታቦት የሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉ በማሳየት ታላቅ የቤተ ክርስቲያኒቱ እና የኢትዮጵያ አባት መሆናቸውን አስረግጦ ያቀርባል፤ ቅዱሱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ አባት መሆናቸውንም ማስረጃ እየጠቀሰ ያሳያል፡፡

በነዚህ ምክንያቶች፣ መጽሐፉ ከሃይማኖታዊ ፋይዳ ባሻገር የሀገራችንን የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ ለመረዳት እጅግ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡ ዘመናዊ የታሪክ ጥናት ሥነ ዘዴን እየተከተለ በተደረገ ምርምር ላይ ተመሥርቶ የተጻፈ የሕይወት ታሪክ ስለሌለ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናንም ሆኑ የታሪክ አስተማሪዎች እና ተመራማሪዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙበት ማጣቀሻ የጻድቁን ገድል (ወይም በገድሉ ላይ የተመሠረተ የታሪክ ድርሳን) ነው፡፡ ከአያሌ ዓመታት ጥናት በኋላ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ያለውን ትልቅ ክፍተት ይሞላል፡፡

ለደራሲው፣ ይህ የታሪክ ጥናት የመጀመሪያው አይደለም፤ ከዚህ በፊት፣ ጥልቅ ምርምር አድርጎ ያሳተማቸው ድርሳናት፡- አራቱ ኃያላን (የአራት የመካከለኛው ዘመን ቅዱሳን ታሪክ) እና እጨጌ እንባቆም፡- ከየመን እስከ ደብረ ሊባኖስ – ለመካከለኛው ዘመን ጥናት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሥራዎች በመሆናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ዕውቅና እያገኙ መጥተዋል፤ ይህ ያሁኑ መጽሐፍ የነዚያ ጥናቶች ተከታይ ቢሆንም፣ ለዲያቆን ዳንኤል እንደ ዐቢይ ሥራው (magnum opus) ሊታይ ይገባዋል፡፡ ምእመናን፣ የታሪክ ሊቃውንት ወይም ሌሎች ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለማወቅ የሚሹ ሁሉ ቢያነቡት ብዙ ጥቅም ሊያገኙበት እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡

ሺፈራው በቀለ፣ ኤመሪተስ ፕሮፌሰር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply