ፖሊስ አቶ ተስፋዬ ኡርጌን በተጨማሪነት በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

መርማሪ ፖሊስ የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት የስራ ባልደረባ አቶ ተስፋዬ ኡርጌን በተጨማሪነት በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስም የቀድሞውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት የስራ ባልደረባ በተጨማሪነት በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

አቶ ተስፋዬ የደህንነት መምሪያ ሀላፊ ሆነው ሲሰሩ ሰዎችን በሽብር ተጠርጥራችኋል በሚል በስውር እስር ቤት በማሰርና በማሰቃየት፥ እርቃናቸውን በካቴና አስረው ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ በማቆየት፣ ግለሰቦችን ባልተገባ መልኩ ለሽብር መልምለው ወደ ኤርትራ በመላክ እንደጠረጠራቸው ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በሽብር ከተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ገንዘብ በመቀበል እና በሀዋላ ከተጠርጣሪዎች ላይ ህገ ወጥ ገንዘብ በመቀበል በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁም ብሏል መርማሪ ፖሊስ።

ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅም 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀን ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

አቶ ተስፋዬ በሰጡት ምላሽ እርሳቸው የተጠረጠሩበት ጉዳይ በግልጽና በተናጠል እንዳልቀረበ በመግለጽ፥ እርሳቸውን ለመያዝ በቂና ዝርዝር ጉዳይ አለመኖሩን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ሀብት የመፍጠር ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሃብት ማፍራታቸውንና ለአራት ወራት ፍርድ ቤት እየተመላለሱ መሆኑን በመጥቀስ፥ ሃብት ከማፍራት ጋር ተያይዞ ሀምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ቤታቸው መበርበሩንና ምርመራው በወቅቱ ማለቅ ነበረበት ብለዋል።

አሁን ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜም ሊሰጥ አይገባም በማለት ተቃውመዋል።

ችሎቱም አቶ ተስፋዬ በተጨማሪነት የተጠረጠሩበት ወንጀል በተብራራ መልኩ እንዲቀርብና ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን በመፍቀድ ለህዳር 24 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። FBC

Share.

About Author

Leave A Reply